መጋቢት 07 ቀን 2014 (ኦርጂን) ‘ኤች አር 6600’ ረቂቅ ህግ የኢትዮጵያንና አሜሪካን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ከማሻከር በተጨማሪ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንከን የሚፈጥር መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትንም ጨምሮ የቆየና ታሪካዊ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሽብር እንቅስቃሴን በመዋጋትና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በጋራ የሚሰሩ አገራት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ አለመግባባቶች ቢኖሩ እንኳን ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የጋራ ትብብርና የቆየ ወዳጅነት አጠናክሮ የመቀጠል ጽኑ አቋም እንዳላትም ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአሜሪካ አስተዳደር ውስጥ የሁለቱን አገሮች የትብብር ግንኙነት የሚያሻክሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
በአሜሪካ የኮንግረስ አባላት የተዘጋጀው ‘ኤች አር 6600’ ረቂቅ ህግ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ለማሳደር የተዘጋጀና የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የሚያሻክር መሆኑን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።
የአሜሪካ ኮንግረስ እንደ ህግ አውጪ ተቋምነቱ የመሰለውን ሐሳብ ቢያራምድም ረቂቅ ህጉ ግን ለሁለቱ አገሮች መልካም ግንኙነት እንቅፋት የሚሆንና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንከን የሚፈጥር ነው ብለዋል።
በአሜሪካ በኩል የሁለቱ አገራት ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር የሚሰሩ እንዳሉም ጠቁመዋል።
በመሆኑም ይህንን ያልተገባ ረቂቅ ህግ ለማውገዝ በተለይም ዳያስፖራዎች በ”በቃ” ንቅናቄ ያሳዩትን ትግል ‘ኤች አር 6600’ እንዳይፀድቅ በመቃወም እንዲደግሙት ጠይቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ረቂቅ ህጉ እንዳይፀድቅ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ የረቂቅ ህጉን ጎጂነት ለሚመለከታቸው የአሜሪካ ተቋማት በማስረዳት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ እውነታውን በመረዳት ኢትዮጵያን የሚደግፉ እንዳሉ በመግለጽ ረቂቅ ህጉ ተገቢ ባለመሆኑ እንዳይፀድቅ እንደሚሰሩ እምነት አለን ብለዋል።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ዳያስፖራዎች ሰሞኑን በኒው ጀርሲ ያሳዩትን ትዕይንተ ህዝብ አስታውሰው በሌሎችም አካባቢዎች እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
አስተያየት ይለጥፉ