ኦርጂን አዲስ አበባ፡- የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ2013/14 ዓ.ም ባስመዘገበው አፈፃፀም የላቀ አገልግሎት ተሸላሚ ሆነ፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ሽልማቱን ማዘጋጀቱን አድንቀዋል።
ሽልማቱ ተቋሙ ለሠራቸው በርካታ ሥራዎች ዕውቅና የሚሰጥና ባለሙያዎችንም ለተሻለ ውጤት የሚያነቃቃ ነው ብለዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅትም ሆነ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተከሰተው ጦርነት ላይ ከሕክምና ባለሙያዎቹ በተጨማሪ የአስተዳደር ሠራተኞችና የአካባቢው ወጣቶች እንዲሁም ከማኅበራት ጋር ተቀናጅቶ ሲሠራ እንደቆየ ገልፀዋል፡፡
እንደ ዶክተር አሸናፊ ገለፃ፤ ባለሙያዎች ወደ ጦርነት ሄደው ሙያዊ እገዛ እንዲሰጡ ከመደረጋቸው በፊት በሥነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ ልዩ ሥልጠና ተሰጥቷል። ዝግጅቱም ጥሩ ውጤት ስለተገኘበት የሕክምና ባለሙያዎች ግንባር ድረስ ዘልቀው የሕክምና እርዳታ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
አስቀድመን ልዩ ዝግጅት በማድረጋችን በጦርነቱ ምክንያት በርካታ የሆኑ ቁስለኞች ወደ ሆስፒታሉ መጥተው ሕክምና አድርገውና ሙሉ ለሙሉ አገግመው መሄድ ችለዋል ብለዋል፡፡
ተቋሙ ለላቀ አገልግሎት ሽልማት የበቃው በአካባቢው ካሉ የጎንደር ከተማ ወጣቶች ጋር በትብብር በመሥራቱ ነው ያሉት ዶክተር አሸናፊ፤ በተለያዩ ወቅቶች በበጎ ፈቃደኝነት ሲያገለግሉ ለነበሩ ለአካባቢው ተወላጆችና የወጣቶች ማኅበራት ምሥጋና አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ተቋሙ ለወደፊቱ በጦርነትም ሆነ የተለያዩ ወረርሽኞች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በማሰብ ተፅዕኖውን ሊቋቋሙ የሚችሉ ሐኪሞችን ለማፍራት እንደሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከአለፉት ፈተናዎች አንጻር ተፅዕኖ ሊቋቋም የሚችል የጤና ባለሙያ ማፍራት እንዳለብን ተምረናል ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንደዚህ ዓይነት ነገሮችን በአጫጭር ሥልጠና ብቻ ሳይሆን በጤና የትምህርት ካሪኩለም ውስጥ ተካተው እንዲሰጡ ለማስቻል ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
በተቋም ደረጃ ከዚህ በፊት የቀውስ ጊዜያት ተብለው በትኩረት ሲሠራባቸው ከነበሩ ጉዳዮች ባለፈ በመሆኑ በመጪው ጊዜ ለመደበኛ ሥራዎች ትኩረት በመስጠት መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ እናተኩራለን፤ በተደጋጋሚ ተሸላሚ ለመሆን እንሠራለን ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በጦርነቱ የተነሳ ጉዳት የደረሰባቸውን ሆስፒታሎች መልሶ ለማቋቋም የተሠራው ሥራ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ዩኒቨርሲቲው ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ የጤና ተቋማትን እየደገፈ መሆኑም ገልጸዋል።
ለተለያዩ ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የሕክምና ዕቃዎችንና መድኃኒቶችን ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በጤና ሳይንስ ኮሌጁና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ አማካኝነት የአስቸኳይ ጊዜና የአደጋዎች ዝግጁነት ማዕከላትን ማቋቋሙን ጠቁመው፤ ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት እንዲሁም ከከተሞች ጋር በመቀናጀት የሚሠራ የዝግጁነት ማዕከል ማዘጋጀቱን ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ በበኩላቸው፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ከወረርሽኝ ቅኝት ጀምሮ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለደረሰ ልዩና የላቀ አገልግሎት እንዲሁም በጦርነት ወቅት ለሠሩት ተመሳሳይ ሥራ የጤናው ሴክተር በመላ ምሥጋና እንደሚገባቸው ገልፀዋል፡፡
አያይዘውም በሁለተኛው የአምስት ዓመት የጤና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ አንዱና ዋነኛው የጤና ባለሙያዎችን ተነሳሽነት ለማሳደግ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ በዚህም መሠረት የጤና ባለሙያዎችን ተነሳሽነት ለመጨመር ከዚህ ቀደም የነበሩ የማትጊያ ሥርዓቶችን በመከለስ ሂደት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር አየለ ገለፃ፤ በሕክምና ማኅበሩ እንዲህ ዓይነት የማትጊያ ሽልማቶች መደረጋቸው የጤና ዘርፉን ለማነቃቃት አጋዢ እንደሆነና በዘርፉ ላይ አወንታዊ ለውጥ ለማምጣት ይረዳል፡፡ የጤና ሚኒስቴር እና የጤና ማኅበራት ቅንጅታዊ ሥራዎች የተሻለና ጥራት ያለው አገልግሎት ለማምጣት አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ሽልማቱን ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር በሙያቸው ለአገር የሚጠቅም ሥራ የሠሩ ግለሰቦችን፣ በጤናው ዘርፍ በዩኒቨርስቲዎች እየተማሩ ጥሩ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችንና የአገልግሎት ጥራት ያስመዘገቡ ተቋማትን በየዓመቱ ይሸልማል፡፡
ይሄን ተጭነው በቴሌግራም ገጻችን ይቀላቀሉን
አስተያየት ይለጥፉ