ኦርጂን አዲስ አበባ፦ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በ705 ሺህ ሕግን በተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ገለጸ፡፡ ኤጀንሲው አዲስ የትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎችን የደንብ ልብስ ይፋ አደረገ፡፡
የኤጀንሲውን ያለፉት ዘጠኝ ወራት የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ክበበው ሚደቅሳ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 705 ሺህ ሕግን ተላልፈው በተገኙ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡
በግንዛቤ የተደገፈ ጥብቅ የትራፊክ ቁጥጥር በማድረግ በትራፊክ ግጭት አደጋ የሚያደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስና ለማስቀረት ተሠርቷል።
ያጋጠሙ ችግሮችን በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ለመፍታት እንደሚሠራም ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኤጀንሲው አዲስ የትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎችን የደንብ ልብስ ይፋ አደርጓል፡፡ ኤጀንሲው ይፋ ያደረገው የትራፊክ ቁጥጥር የደንብ ልብስ የቁጥጥር ስራውን ለማጠናከርና የተመሣሣይ አንፀባራቂ ልብስ በመልበስ የተሽከርካሪ ዘረፋና ሌብነት ተግባርን ለመቅረፍ የሚያግዝ ነው ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የኤጀንሲው የቁጥጥር ባለሙያዎች እና የሚያከናውናቸው ተግባራት በከተማዋ በተለይ ሰሞኑን እየተስተዋለ የሚገኘው በአንድ ጊዜ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘውን አደጋ ለመቀነስ እና ለማስቀረት ነው።
ኤጀንሲው ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ትራፊክ ፖሊሶች ጭምር የሚሆኑ ጠጥቶ ማሽከርከርን ለመቆጣጠር የሚረዱ 100 ሺህ የትንፋሽ መፈተሻ እና 10 የአልኮል መጠጥ መመርመሪያ መሣሪያዎች፣ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ራዳሮች፣ የትራፊክ ግጭት አደጋዎች ወቅት የሚያገለግሉ ኮኖች፣ ቾክ እና የመሳሰሉትንም እያሟላ መሆኑን ተናግረዋል።
የኤጀንሲው የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የትራፊክ ማስተናበርን ጭምር በንድፈ ሀሳብ እና በተግባር የተደገፈ ስልጠና ወስደው አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ናቸው ብለዋል።
ከፊታችን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት በሚከበረው ፋሲካ በዓል ወቅት ከፍተኛ የትራፊክና የሕዝብ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ታሳቢ ያደረገ በአሽከርካሪውና እግረኛው በኩል ተገቢ ጥንቃቄ እንዲደረግም አሳስበዋል።
የብዙኃን ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች የትራፊክ ሕግን እና ደንብን አክብረው እንዲያሽከረክሩ፣ እግረኞችም ተገቢውን የመንገድ ደህንነት ጥንቃቄ በማድረግ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ኅብረተሰቡን በማስተማር እና አስፈላጊ መረጃዎችን ወደ ሕዝብ በማድረስ ከኤጀንሲው ጋር በትብብር እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።
የብሉምበርግ ኢኒሺየቲቭ የመንገድ ደህንነት የዳታ ምርመራ ባለሙያ ወይዘሮ ሜሮን ጌታቸው በበኩላቸው በወቅቱ እንዳሉት፤ ከሐምሌ 2013 ዓ.ም እስከ ታኅሳስ 2014 ዓ.ም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት አንጻር የትራፊክ ሞት አደጋ በአምስት በመቶ የአካል ጉዳት ደግሞ በአስር በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
በከተማዋ ከአምስት የትራፊክ አደጋ ሞት ውስጥ አራቱ የሚደርሰው በእግረኞች ላይ ሲሆን ባለፉት ዓመታትም በተመሳሳይ የታየ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በትራፊክ አደጋ በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ሞት ያስተናገደው ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ ሲሆን ቦሌ ሚካኤል ደግሞ በሁለተኛነት ተቀምጧል።

አስተያየት ይለጥፉ