ሩሲያ እና ዩክሬን ጀምረውት የነበረውን ንግግር ሊቀጥሉ ነው

 

ጦርነት ላይ የሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬን ጀምረውት የነበረውን ንግግር ሊቀጥሉ መሆኑ ተገለጸ።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ጦርነቱ ወደጎረቤት አገራት ሊስፋፋ ይችላል ሲሉ ሰግተዋል። በቤላሩስ እና በቱርክ የሰላም ንግግር ጀምረው የነበሩት አገራቱ ለመገናኘትና ንግግር ለማድረግ እንዳቀዱ ተገልጿል።

ሩሲያ ከትናንት በስቲያ በፖላንድ አቅራቢያ ጥቃት ማድረሷን ተከትሎ ጦርነቱ ከሁለቱ አገራት አልፎ ወደ ሩሲያ እና ኔቶ እንዲሁም ወደ ሙሉ አውሮፓና ሩሲያ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት ሲነሳ ነበር።

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከዩክሬኑ አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር በቱርክ በአካል መገናኘታቸው የተገለጸ ቢሆንም ንግግራቸው ግን ውጤት አላመጣም ተብሏል።

ኪዬቭ እና ሞስኮ በተወካዮቻቸው በኩል ንግግር ያደርጋሉ ይባል እንጂ የትና በየትኞቹ ተወካዮቻቸው በኩል እንደሚገናኙ ግን በዝርዝር አልተገለጸም።

ሲጂቲኤን በበኩሉ የክሬምሊን ቃል አቀባይ የሆኑትን ዲሚትሪ ፔስኮቭ ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ የሩሲያ እና የዩክሬን ተወካዮች ውይይታቸውን በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንደሚያደርጉ ዘግቧል። እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፤ በውይይቱ የፕሬዚዳንት ቭላድሚር

ፑቲን አማካሪ ቭላድሚር ሜዲንስኪ የሩሲያ ልዑክን ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል። የዴቪድ አራካሚያ ደግሞ የዩክሬንን ልዑክ ይመራሉ ነው የተባለው።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ዜለንስኪ ቀደም ሲል ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት የኪዬቭ ተወካዮች የተሳካ ውይይት እንዲደረግ የተቻለውን ሁሉ ጥረት ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቀናት በፊት ለፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ከጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሹልዝ ጋር በስልክ ባደረጉት ንግግር በቅርብ ቀናት ውስጥ በሩሲያ እና በዩክሬን ተወካዮች መካከል በቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይቶች እንደሚኖሩ ገልፀው ነበር።

ሩሲያ እና ዩክሬን እስካሁን ሶስት ዙር የፊት ለፊት ውይይት በቤላሩስ ያካሄዱ ሲሆን ሁሉም ውይይቶች ያለስምምነት መጠናቀቃቸውን ይታወሳል።

አሜሪካንና ኔቶን በተደጋጋሚ እየተማጸኑ ያሉት የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ አሁን በሁለቱ አገራት መካከል የተጀመረው ጦርነት ወደ ጎረቤት አገራት ሊስፋፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በዚህም መሰረት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) ወደ ዩክሬን አውሮፕላን እንዳይበር ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል።

ኔቶ እና አሜሪካ ቀደም ሲል በዩክሬን አውሮፕላን እንዳይበር ማድረግ ጦርነቱን ሊያስፋፋው እንደሚችል ከገለጹ በኋላ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ኔቶን “ደካማና የማይጠቅም” በሚል መዝለፋቸው ይታወሳል።

ይህንን ዘለፋ ተከትሎ የኔቶ ዋና ጸሐፊ ጆንስ ስቶልተንበርግ የሰጡት ስለመኖሩ አልተገለጸም።

ባሳለፍነው ሳምንት ሩሲያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ስብሰባ እንዲያደርግ መጠየቋን አስታውቃ ነበር።

ሞስኮ ስብሰባው እንዲጠራ የፈለገችው በአሜሪካ እንደሚደገፍ በገመተችውና በዩክሬን አለ በተባለው የስነ ሕይወታዊ ጦር መሳሪያ (ባየሎጂካል ዊፐን) ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል።

Post a Comment

አዲስ የድሮ