ፌደራል ፖሊስ ከሁለት ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በተለያዩ ዘርፎች ለመስራት ተስማማ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2014 (ኦርጂን) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከአውሮፓ ህብረት የጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጂ.አይ.ዜድ) እና የጄኔቫ የፀጥታ ዘርፍ አስተዳደር ማዕከል (ዲካፍ) ጋር በፎረንሲክ ምርመራ ቴክኖሎጂዎችን ለማሟላት እና በስልጠና ዙሪያ አብሮ ለመስራት ተስማማ፡፡

ስምምነቱ የተደረሰው የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ የፀጥታ ዘርፍ ሪፎርም እንዲደግፉ ያቋቋማቸው የቴክኒክ ልዑካን ቡድንን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ በዋናው መስሪያ ቤት ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።

ከጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ እና የጄኔቫ የፀጥታ ዘርፍ አስተዳደር ማዕከል የተውጣጡ የቴክኒክ ልዑካን ቡድን ባነጋገሩበት ወቅት

የቴክኒክ ቡድኖቹ እስከአሁን ለኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስ እያደረጉ ያሉትን የቁሳቁስና የስልጠና ድጋፍ ኮሚሽነር ጄነራል አመስግነው ፥ እንደ ሀገር የተጀመረውን የፀጥታ ዘርፍ ማሻሻያ ፕሮግራም ተከትሎ ተቋሙን ከነበረበት ወደ ተሻለ አቅም ለማድረስ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል፡፡

ኮሚሽነር ጄነራሉ አያይዘውም ፥ ተቋሙ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ውጤታማ ስራዎች ማከናወን መቻሉን በመግለፅ ከዚህ ቀደም ሲወቀስበት የነበረውን ማዕከላዊ የወንጀል ምርመራን በመዝጋትና የተጠርጣሪ ማቆያ ቦታን ለአያያዝ ምቹ በማድረግ እንዲሁም የምርመራ ሂደቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብት ባከበረ አኳኋን በሳይንሳዊ መንገድ ምርመራ እንደሚከናወን ለልዑካን ቡድኑ አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ በማስቀጠል ተቋሙን በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አምስት የፓሊስ ተቋማት አንዱ ለማድረግና በአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ የያዛቸውን ግቦች ለማሳካት እንዲህ ዓይነቱ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስ ከኬኒያ፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከጅቡቲ ፓሊስ ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልፀው ፥ የቴክኒክ ቡድኖቹ ለተቋሙ የሚያደርጉት ድጋፍ ድንበር ተሻጋሪና ውስብስብ የሆኑ ወንጀሎችን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀንድ ጭምር ለመከላከል የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ም/ኮሚሽንር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ በበኩላቸው ፥ ባለፉት ሦስት ዓመታት የምርመራ አቅምን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የተለያዩ የዲ.ኤ.ንኤ ማሽኖችን የማሟላት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ቢሮው የፎረንሲክ ስትራቴጂን ከስረ መሰረቱ በመቅረፅ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ ተወካይ ኔይል ፔጅ በበኩላቸው ኮሚሽነር ጄነራሉ የወንጀል ምርመራ ቢሮውን ለማዘመንና ለማጠናከር የሰጡትን ትኩረት አድንቀው ፥ በፎረንሲክ ምርመራ፣ የምርመራ አቅምን በሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች እና ስልጠናዎች ተቋሙን የበለጠ ለማገዝ በትኩረት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።

የድጋፍ ፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስን የፎረንሲክ ስትራቴጂ ካላቸው አራቱ የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዱ እንደሚያደርገው ገልፀው ፥ በዲ.ኤን.ኤ፣ በፈንጂ እና በእሳት አደጋ ምርመራዎች እንዲሁም የሳይበር ጥቃትን መለየትና መከላከል የሚያስችሉ መሳሪያዎች፣ በፎረንሲክ ቶክሲኮሎጂና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን መመርመር የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተወካዩ ቃል ገብተዋል።

ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ ከጂ.አይ.ዜድ እና ከዲካፍ የተውጣጣ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ በቅርብ ቀን እንደሚጀምር መግባባት ላይ መድረሳቸው ታውቋል።

የተደረገው ስምምነት ተቋሙን በፎረንሲክ የምርመራ ዘዴ አንድ እርምጃ ወደ ፊት እንደሚያራምደውና የምርመራ አቅሙን ለማሳደግ ትልቅ ዕድል እንደሚከፍትለት ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኦርጂን በቴሌግራም ይቀላቀሉን ፤

Post a Comment

አዲስ የድሮ