አዲስ አበባ ፳፭ ቀን ሚያዚያ ፳፼፲፬ ዓ.ም (ኦርጂን)
አሸባሪው ሕወሓት ቡድን እራሱ የፈጠረውን ችግር አሁንም በኃይል እፈታዋለሁ በሚል የሚያደርገው ዳግም የጦርነት ቅስቀሳና ዝግጅት በትግራይ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ቀውስ ለመፍጠር መሆኑን ራእይ ፓርቲ መሥራችና ሊቀመንበር አቶ ሊላይ ኃይለማርያም ገለጹ፡፡ ቡድኑ በቂ ወታደራዊ ስልጠና ያልነበራቸውን ወጣቶች ወደ ጦርነቱ መማገዱን ማመኑንም አመልክተዋል፡፡
አቶ ሊላይ ኃይለማርያም ለወጋህታ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የሕወሓት ቡድን መሪዎች ችግሩን በኃይል እንፈታዋለን የሚሉት ለትግራይ ሕዝብ ችግር
ስለማይጨነቁና ደንታ ስሌላቸው ነው። የትግራይ ሕዝብ በሕወሓት ምክንያት እየተጎዳ ቢሆንም አሁንም ቡድኑ በትግራይ ሕዝብ ችግር ላይ ተጨማሪ ቀውስ ለመፍጠር የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ነው።
የፌዴራል መንግሥት ለሰላም እጁን ቢዘረጋም፣ ሕወሓት ሰላም የሚፈልግ ኃይል አይደለም ያሉት አቶ ሊላይ፤ ሕወሓት ሲፈጠር ጀምሮ ችግሮችን በሰላም ፈትቶ አያውቅም፤ ባህሪውም የሚፈቅድለት አይደለም። ከዚህ በፊትም ብዙ ፖለቲካዊ ድርጅቶችን በኃይል እያጠፋ የመጣ ኃይል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ አቶ ሊላይ ገለፃ፣ ሕወሓት ችግሮችን በሰላም የመፍታት ፍላጎት የለውም፤ ሲፈጠር ጀምሮ በድርድር አያምንም። በሕወሓት ቤት የተለየ ሀሳብ ካነሳህ የሚጠብቅህ ሞት፣ ስቅላትና እስራት ነው፤ ከድሮ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይህን ባህሪው እንደተጠናወተው ይገኛል።
ከአፈጣጠሩ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስም በኃይል እንጂ በድርድር የፈታው ችግር እንደሌለ ተናግረዋል።
አሁንም ከመንግሥት ያለው ችግር በሰላም ከመፍታት ይልቅ በኃይል እፈታዋለሁ ማለቱ ከባህሪው የሚመነጭ መሆኑን አውስተው፤ ምክንያቱም ችግሮች በሰላም ለመፍታት ባህሪው አይፈቅድለትም። ከባህሪው አንፃር ከሕወሓት ጋር በሰላም የሚፈታ ችግር እንደሌለና ሁሉም ነገር በጦርነት መፍታት የሚፈልግ ቡድን መሆኑን አመልክተዋል።
ሕወሓት በፈጠረው ችግር ብዙ የትግራይ ወጣት ሞቷል። ሕዝቡም ለከፋ ችግር ተዳርጓል፤ ወደ አጓራባች ክልሎችም እየተፈናቀለ ይገኛል ያሉት አቶ ሊላይ፤ አሁን ሕወሓት በአዲስ መልክ ጦርነት እጀምራለሁ የሚል ከሆነ በትግራይ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ ቀውስ ከመፍጠሩ በተጨማሪ ለራሱ የመጨረሻ መጥፊያው መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ በፊት በሕዝብ የተገኘው ድል ሕወሓት ለራሱ ጥቅም እንዳዋለው አውስተው፤ አሁንም ለራሱ ጥቅም ሲል የትግራይን ሕዝብ ወደ ችግር እየከተተው መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁንም ቡድኑ በፈጠረው ችግር ምክንያት ሕዝቡ አላስፈላጊ ዋጋ እየከፈለ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ ከሕወሓት ጭቆና ነፃ ለመውጣት እየታገለ ቢሆንም ቡድኑ ሕዝብን በመከፋፈልና ነፃነት በመንፈግ የችግሩ ሰለባ እያደረገው እንደሚገኝ ገልጸው፤ ከቡድኑ ጨቋኝ ሀሳብ ያፈነገጡ ሰዎችን እየደበደበና እያሰረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የትግራይ ሕዝብ የኢትዮጵያ አካል በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ከሌሎች ፖለቲካዊ ፓርቲዎች ጋር በመሆን ነፃ ሊያወጡት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ዋጋ የከፈለ ሕዝብ ነው ያሉት አቶ ሊላይ፤ ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ጭምር መሆኑ ተናግረዋል።
የሕወሓት አመራር ቡድን በቅርብ ጊዜ ከምሁራን ጋር ውይይት አድርገዋል ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያ የተላለፈ የድምጽ መልዕክትም በጦርነት ወቅት በቂ ስልጠና ያልወሰዱ ወጣቶች በጦርነቱ ማሳለፋቸውንና አሁንም ለጦርነት እየተዘጋጁ መሆኑን መናገራቸውን ታውቋል።
በአማራና አፋር ክልሎች ደግሞ ዝርፊያ እንደፈፀሙ ማመናቸውንና የቡድኑ አመራሮችም አሁንም ለጦርነት መዘጋጀታቸውም ለሁለተኛ ጊዜ የትግራይ ወጣት እንዲያልቅ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያመላክት መሆኑን አቶ ሊላይ ጠቅሰዋል።

አስተያየት ይለጥፉ