አዲስ አበባ ፣ ፲፪ ቀን ሚያዝያ ፳፼፲፬ (ኦርጂን)
የአፍሪካ አገራት ደመና የማበልጸግ ቴክኖሎጂን በዘርፉ ውጤታማነቷን ካሳየችው ኢትዮጵያ ሊማሩ ይገባል ሲሉ በዓለም የሜቲዮሮሎጂካል ተቋም የአፍሪካ አህጉራዊ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሞስ ማካራው ተናገሩ።በዓለም የሜቲዮሮሎጂ ተቋም አህጉራዊው ማህበር አንድ (RA I) የማኔጅመንት ቡድን ለሁለት ቀናት የሚቆየውን ስብሰባ ትናንት በአዲስ አበባ ጀምሯል። በወቅቱ ዶክተር አሞስ ማካራው እንዳስታወቁት፤ ኢትዮጵያ ደመናን በማበልጸግ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው። ከዚህ ሳይንሳዊ ሥራ በርካታ የአፍሪካ አገራት ልምድ መቅሰም ይኖርባቸዋል።
ደመናን በማበልጸግ (Cloud Seeding) ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለው ርቀት ውጤታማ አድርጓታል ያሉት ዶክተር አሞስ፤ የዚህ አይነቱ ቴክኖሎጂ ትግበራ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን የድርቅ አደጋ ለመቋቋም አንዱ አማራጭ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ተፈጥሯዊ ዳመናን ወደ ዝናብ በመቀየርም ሆነ ሰው ሰራሽ ደመናን በማበልጸግ የሚከናወነው ተግባር በድርቅ ለሚጎዱ የአፍሪካ አገራት ተጨማሪ የውሃ አማራጭ እንዲያገኙ ይረዳል ብለዋል።
በአፍሪካ ያሉ ወደብ አልባ አገራት ቴክኖሎጂውን በይበልጥ መጠቀም እንዳለባቸው የጠቆሙት ዶክተር አሞስ፤ እነዚህ የአፍሪካ አገራት በተለይ ከአየር ንብረት መለዋወጥ ጋር ተያይዞ በሚከሰት ተደጋጋሚ ድርቅ ይጠቃሉ። አገራቱ ደግሞ ከውቅያኖሶች ያላቸው ርቀት ረጅም በመሆኑ የውቅያኖሱን ውሃ በማጣራት በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚያውሉበት አማራጭ እንደሌላቸው ገልጸዋል።
ደመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ በሰው ሰራሽ መንገድ የሚገኘውን የዝናብ ውሃ ተጠቅመው በድርቅና የተለያዩ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ጥረት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
የአፍሪካ አገራት በየዓመቱ ከሚያገኙት ተፈጥሯዊ ዝናብ ባለፈ ቴክኖሎጂውን ተጠቅመው ተጨማሪ የዝናብ ውሃን መሰብሰብ ይችላሉ። በዚህም ለግብርና ሥራም ሆነ ለተለያዩ አገልግሎቶች መጠቀም የሚችሉበት ዕድል ቀርቦላቸዋል ብለዋል።ከዚህ ባለፈ የአፍሪካ አገራት በዝናብ ዕጥረት ምክንያት የሚደርስባቸውን የግድቦች ውሃ መጠን መቀነስና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታትም ዳመናን የማበልጸግ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።
በዚህ ረገድ ደግሞ ኢትዮጵያ የተሻለ ልምድና ውጤት ማግኘቷን በተግባር አሳይታለች ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ልምዱን መቅሰም የሚፈልጉ ታዳጊ የአፍሪካ አገራትን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የተለያዩ ስልጠናዎችን መውሰድ ይገባቸዋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት እያሳየ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው ያሉት ዶክተር አሞስ፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረትም ለሌሎችም አገራት ተሞክሮ መሆን የሚችል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከደመናን ማበልጸግ በተጨማሪ ለሜቲዮሮሎጂ አገልግሎት የሚታገዝ ሳተላይት ማምጠቅ መቻሉ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ይህን አይነት ልምድ ሌሎች አገራትም ሊከተሉት ይገባል ብለዋል።አፍሪካውያን ችግሮቻችንን ተረዳድተን ማለፍ ይጠበቅብናል፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂውን ለመቅሰም የሚፈልጉ አገራት ሲገኙ ትብብር ማድረግ ይኖርባታል ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ድርቅ በሚከሰትባቸው ስፍራዎች ደመናን በማበልጸግ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ እንዴት የዝናብ ውሃ ማግኘት ይቻላል? በሚሉና ተያያዥ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የእርስ በርስ ድጋፍ በመሰጣጣት የአፍሪካ አገራት በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል።ኢትዮጵያ የደመና ማበልጸግ ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ለማዋል በምታከናውነው ተግባር ድሮኖችን ጥቅም ላይ እያዋለች እንደሚገኝ ታውቋል።

አስተያየት ይለጥፉ