አዲስ አበባ ሚያዝያ ፲፪ ፣ ፳፼፲፬ ዓ.ም (ኦርጂን)
ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የሀገራቸውን የተፈጥሮና የባህል ሀብቶች ለለውጥ በመጠቀም ሀገራቸውን ለማሳደግ ዝግጁ እንዲሆኑ የዓለም አቀፍ ወጣቶች ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ቹ ሱንግ ሁዋ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ለተወጣጡ ወጣቶች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቋል።
ሥልጠናው በዋናነት ወጣቶች ምክንያታዊ እንዲሆኑ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ለሀገራቸው ያላቸው እይታ እንዲሻሻል የሚረዱ ሐሳቦችን ያካተተ ነው ተብሏል።
በማጠቃላይ መርሃ-ግብር ላይ የተገኙት የዓለም አቀፍ ወጣቶች ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ቹ ሱንግ ሁዋ፣ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት፣ በባህልና በሌሎች ሃብቶች የታደለች መሆኗን መስክረዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች እነዚህን የተፈጥሮና የባህል ሀብቶች ለለውጥ በመጠቀም ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለማሳደግ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ዶክተር ቹ የትውልድ ሀገራቸው ኮሪያ ከዓመታት በፊት እርስበርስ በመከፋፈል ጦርነት ውስጥ በመግባት ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ተብላ ለሁለት መከፈሏን አንስተዋል።
”ይህ መከፋፈል ለጠላቶቻችን ካልሆነ በስተቀር ለኮሪያዊያን የጠቀማቸው አንዳች ነገር የለም” ያሉት ዶክተር ቹ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ከኮሪያ ተሞክሮ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።
ለሀገር እድገት ዋና ችግር ሆኖ የሚስተዋለውን እርስበርስ መከፋፈልና አለመከባበር ማስወገድ ከተቻለ ኢትዮጵያ ለእድገት ምቹ ሀገር ናት ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ወጣቶችን በስፋት ወደ ልማትና እድገት ለማምጣት የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ የጀመረውን ሥራ ማጠናከር እንዳለበትም ነው የገለጹት።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው፤ የተሰጠው ሥልጠና ምክንያታዊ ወጣት ለማፍራትና የሥራ እድል ፈጠራን ለማበረታታት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ሥልጠናው በዋናነት ወጣቱ ሥራ ሳይንቅ ራሱን በመለወጥ ሀገሩን ማሳደግ እንደሚችል ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሥልጠናው ወጣቶች የከተማዋንና የሀገሪቱን ሰላም በመጠበቅ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የራሱ አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
በሥልጠናው ተሳታፊ የነበሩ ሰልጣኞችም በቆይታቸው ራሳቸውን መለወጥ የሚያስችል ግንዛቤ እንዳገኙበት ገልጸዋል።
በተለይ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ የተሰጠው ሥልጠና ወጣቶች ጠባቂ ከመሆን ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ መንገድ ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህ ሥልጠና ከሁሉም ክፍለ ከተማ የተውጣጡ ወጣቶች ተሳታፊ ሆነዋል።


አስተያየት ይለጥፉ