‹‹አገልግሎት አሰጣጥ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ስርዓት ይዘረጋል››- የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ:- ሰላም ለማስፈንና ጸጥታን ለማስከበር ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ የህግ የበላይነትን ለማስከበር እንዲሰራ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱ የሚታዩ ብልሽቶችን ለማስተካከል አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ የተውጣጡ ነዋሪዎች ከብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህና ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ትናንት ውይይት አካሂደዋል፡፡
ሥራ አጥነትን፣ የኑሮ ውድነትና ግሽበትን ለመቀነስ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው ተወያዮቹ ጠይቀዋል፡፡ በርካታ እናቶች ወደ ጤና መድህን እንዲገቡ ቢደረግም በሚገባው ልክ እየተጠቀሙ ባለመሆናቸው መፍትሄ እንዲሰጥም በውይይቱ ላይ አንስተዋል፡፡
የጎዳና ተዳዳሪዎች ጉዳይ ትኩረት ይፈልጋል፣ የቤት ኪራይ ዋጋ መናርም መታየት አለበት ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡ በሥራ ላይ ያለው ሰንደቅ ዓላማም ወደቀድሞው እንዲመለስና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግርም እንዲስተካከል በውይይቱ ተጠይቋል፡፡
በሕብረተሰቡ መካከል የተፈጠሩ አለመተማመኖችን ለማረምም ከሃይማኖት ተቋማትና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር መስራት ይገባል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ አንድነትን፣ መተባበርንና መተጋገዝን የማይፈልጉ አካላትን ለማጋለጥ ከመንግሥት ጋር እንደሚሰለፉም ቃል ገብተዋል፡፡
ሰሞኑን የተለቀቀው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት የቀጣይ ትውልድን ተስፋን ያጨልማል ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ጉዳዩ ታይቶ እልባት እንዲሰጠውና የትምህርት ስርዓቱ ትኩረት እንዲደረግበትም ጠይቀዋል፡፡
የቀደመው አይነት ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን በአንድ አካባቢ ሰዎች የመያዝ አባዜ ሊታረሙ የሚገባቸው ናቸው ብለው ካነሷቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አደም ፋራህ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ አገልግሎት አሰጣጥ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው ስርዓት ማስፈን እንደሚገባና ለዚህም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
አገራዊ መግባባት ሊፈጠርባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች አሉ ያሉት አቶ አደም፤ የሰንደቅ ዓላማ፣ የትርክትና መሰል ጉዳዮች ሕብረተሰቡ ተወያይቶባቸው እንዲወስንና እንዲፈቱ ታስቦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙን አስታውሰዋል፡፡
ጽንፈኝነትና አክራሪነትን መታገል ይገባል፣ አግላይና የሚያራርቁ ጉዳዮችን ለማረም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ ያለፈ ጉዳይ ላይ መጣላት አይገባም፣ ለዛሬና ለነገ የሚጠቅመው ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ሕዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እቅዶችን እንደሚተገብርም ቃል ገብተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተወያዮቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ ተመሳሳይ ውይይቶች እስከታችኛው መዋቅር እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል፡፡ የተነሱ ችግሮችና ጥያቄዎች በአንድ ጀንበር ላይፈቱ ቢችሉም ደረጃ በደረጃ መፍትሄ ይሰጣቸዋል፣ አንዳንዱን በአፋጣኝ ስር የሰደደው ደግሞ በሂደት እንደሚቀረፍም አመላክተዋል፡፡
የመንግሥት ሠራተኞች በታማኝነትና በቅንነት ማገልገል ይገባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እኩል የሚያገለግል፣ ኢትዮጵያን የሚመስልና የሚያጸና አንድነት እንደሚገነባም ቃል ገብተዋል፡፡
የፖለቲካ ስብራቶች እንዲጠገኑ ሕብረተሰቡን ያማከለ ሥራ እንደሚሠራ የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች፤ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ዘላቂ ሰላም ማስፈን ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ትግበራው ሕብረተሰቡን ያማከለ ይሆናልም ብለዋል።
አብሮ የመኖር እሴትን ለማጎልበት የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን በመጠቆምም፤ የዜሮ ድምር የፖለቲካ ችግሩ ተጽእኖ መፍጠሩንም ተናግረዋል። አግላይነት፣ በብሔርና በፖለቲካ አመለካከት መገፋፋት የፖለቲካ ጉዞው ችግር መሆናቸውንም አመላክተዋል።
የኑሮ ውድነትና ግሽበትን ለመቆጣጠር ይሠራል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ችግሩን ለመቅረፍ አቅርቦትን ማሳደግ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ተሞክሮው እንዲሰፋ ይደረጋልም ብለዋል፡፡
የንግድ ሚዛኑን የሚያዛቡ ነጋዴዎችን በማረም የንግድ ስርዓቱን ለማስተካከል ቁጥጥር ይደረጋል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሽቱን ለማረምም መንግሥት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ቤተ እምነቶች፣ ልሂቃን፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ጋዜጠኞች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች ከችግሮቹ ለመውጣት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባልም ነው ያሉት።

አስተያየት ይለጥፉ