ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ከቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ


 መጋቢት 06 ቀን 2014 (ኦርጂን) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር ዡ ቢንግ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም አቶ ደመቀ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት እና ቻይና ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለገብ ድጋፍ አድንቀዋል።

ቻይና ለአፍሪካ አህጉር ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ያደነቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቻይና አፍሪካ የትብብር ማዕቀፍ የቀረቡትን የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ይሁንታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር ዙ ቢንግ በበኩላቸው ቻይና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን የፀጥታ፣ የልማት እና የአስተዳደር ፈተናዎችን ለመፍታት እና የአንድነት እና ራስን የማሻሻል ጎዳና እንዲከተሉ መደገፍ ትፈልጋለች ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የቀጣናው መልሕቅ ሀገር እንደመሆኗ መጠን ሰላምን በማስፈን ረገድ ገንቢ ሚና እንዳላት ልዩ መልዕክተኛው መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ኢትዮጵያ እና ቻይና ግንኙነታቸውን ወደ አጠቃላይ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት እ.ኤ.አ በግንቦት 2017 ከፍ አድርገዋል።

ኦርጂን በቴሌግራም ይቀላቀሉን ፤

Post a Comment

አዲስ የድሮ