መጋቢት 07/2014 (ኦርጂን) ከውጭ የተገዛ 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ሊትር ፓልም ዘይት አዲስ አበባ መድረሱን የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ገለጸ።
የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ፤ የገንዘብ ሚኒስቴር ከውጭ የገዛውን ፓልም ዘይት በአጭር ጊዜ ከወደብ ሙሉ ለሙሉ አጓጉዞ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግስት 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት ከውጭ እያስገባ መሆኑን ገልጸው በባቡር ትራንስፖርት የማጓጓዝ ስራው እየተቀላጠፈ መሆኑን ገልጸዋል።እስካሁንም በሁለት ዙር 4 ነጥብ 8 ሚሊየን ሊትር ዘይት ከወደብ ወደ አዲስ አበባ ተጓጉዞ አዲስ አበባ ወደ መጋዘን እየተራገፈ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የዘይት አቅርቦቱን በባቡር የማጓጓዝ ተግባር በፍጥነት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም 3ኛው ባቡር ጅቡቲ ላይ እየጫነ ሲሆን በሚቀጥለው አንድ ሳምንት ውስጥ 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትሩ ዘይት ሙሉ ለሙሉ ተጓጉዞ ይጠናቀቃል ብለዋል።
የዘይት ምርት አቅርቦትና የዋጋ መናር ችግርን ለመፍታት በመንግስት እየተወሰዱ ስላሉ ርምጃዎች ዙሪያ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
በዚህም በሚቀጥሉት ሶስት ወራት 150 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በመንግስት የልማት ድርጅቶች በኩል አፋጣኝ ግዥ ተከናውኖ አገር ውስጥ ይገባል ብለዋል።
የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት አምራቾችን አቅም ለማሳደግም አፋጣኝ የማምረትና የውጭ ምንዛሬ ድጋፍ እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።
አስተያየት ይለጥፉ