ከምትሠራበት ቤት ሁለት ሕፃናትን ሰርቃ የተሰወረችው የቤት ሠራተኛ ከነተባባሪዎቿ ተያዘች

ሁለት ሕፃናትን ከምትሠራበት ቤት ይዛ የተሰወረችው የቤት ሠራተኛና ለወንጀሉ ተባብሯታል ከተባለው ፍቅረኛዋ ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ወንጀሉ መፈጸሙን ለሪፖርተር የገለጸው በኦሮሚያ ክልል የሰበታ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የክፍለ ከተማ 3 ፖሊስ መምሪያ ነው፡፡ መምሪያው እንዳስታወቀው ለሁለት ቀናት ታግተው የቆዩት ሁለት ሕፃናት ነፃ ወጥተዋል፡፡ ሕፃናቱን በማገት 1.5 ሚሊዮን ብር ከወላጆች ለመቀበል ሞክረዋል ተብለው የተጠረጠሩትን የቤት ሠራተኛዋንና የወንጀል ተባባሪዎቿን እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር በማዋል ተጨማሪ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ የፖሊስ መምሪያው አዛዥ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ተጠርጣሪዋ ወ/ሮ ሱሴ አጀማ የአቶ ዘይኑ ሽኩርና ባለቤታቸው ወ/ሮ ፈቲያ ከድር የቤት ሠራተኛ ሆና ስትሠራ መቆየቷን ፖሊስ ገልጿል፡፡ የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ግን ልጆቹን ይዛ በወጣችበት ሳትመለስ ቀረች ይላሉ የሰበታ ፖሊስ ክፍለ ከተማ 3 ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ጉታ ቶሎሳ፡፡ የወንጀሉን አፈጻጸምም ሲያስረዱ፡፡ ‹‹ሠራተኛዋ ሱሴ አጀማ የምትሠራበት ቤት ልጆች የሆኑትን አንደኛ የዘጠኝ ወር ሕፃን ኢብራሂም ዘይኑና ታላቅ እህቱን የአራት ዓመት ታዳጊዋን ተምሲና ዘይኑ የተባሉ ልጆችን ግብረአበሯ አቶ ታሪኩ አሰፋ የተባለው ሁለተኛ ተጠርጣሪ በነገራት መሠረት ከቤት በመውሰድ ደብቃለች፤›› ብለዋል፡፡

ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ሕፃናቱን ከሰበታ ከተማ ቀበሌ 03 ወለቴ ልዩ ቦታው ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ከሚገኘው የወላጆቻቸው ቤት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዘነበ ወርቅ አለርት ሆስፒታል አካባቢ በተከራዩት መኖሪያ ቤት ወስደው መደበቃቸውን ረዳት ኢንስፔክተር ጉታ ይናገራሉ፡፡ ፖሊስ ባደረገው የተቀናጀ ክትትል ሁለቱ ሰዎች አገኘሁ ሞላና ተሾመ አርኖ ከተባሉ ተባባሪዎች ጋር በመሆን ከልጆቹ ወላጆች ከእገታ ማስለቀቂያ ገንዘብ ለመቀበል ሲደራደሩ እንደነበር ረዳት ኢንስፔክተሩ ገልጸዋል፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲሁም ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነትና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት በተደረገ ክትትል ፖሊስ ከሁለት ቀናት የአጋች ታጋች ድራማ በኋላ ልጆቹን ማስለቀቅ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

የልጆቹን እገታ በቅርበት እንደሚያውቁና በፍለጋው ሒደት ሲሳተፉ እንደነበር የጠቀሱት የወላጅ አባት የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አብዱልሀዲ ሰዒድ ሁኔታው ምን መሳይ እንደነበር ከጅምሩ ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡ ወላጆች ሠራተኛ ሲያፈላልጉ ቆይተው ታኅሳስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም.  መርካቶ ከረሜላ ፋብሪካ አካባቢ ባሉ ደላሎች አማካይነት ሱሴ አጀማ የተባለችውን የቤት ሠራተኛ ማግኘታቸውን የሚናገረው አብዱልሀዲ ከቤተሰቡ ጋር ተላምዳ ስትሠራ እንደቆየች አስረድቷል፡፡ ሆኖም የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. አመሻሽ 11 ሰዓት አካባቢ ሱቅ ደርሼ ልምጣ ብላ ያዘለችውን ሕፃንና አንዲት ታዳጊ ይዛ ከቤት እንደተሰወረች ይናገራል፡፡ የዛኑ ዕለት ከምሽቱ 1 ሰዓት ለወላጆች ስልክ መደወሉንና ልጆቻቸው መታገታቸው እንደተነገራቸው ያስረዱት አቶ አብዱልሀዲ 1.5 ሚሊዮን ብር ልጆቹን ከእገታ ለማስለቀቅ ክፈሉ መባላቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በማግሥቱ ጠዋትም ተመሳሳይ የማስፈራሪያ መልዕክት ለወላጆች መድረሱን ያመለከቱት አቶ አብዱልሀዲ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ጉዳዩን በማመልከት መላው ቤተሰቡና ዘመድ ወዳጆች ልጆቹን ለማፈላለግ መነሳታቸውን ገልጸዋል፡፡ የአጋቾቹን ስልክ የመደወያ አድራሻ ለማወቅ በተደረገው ጥረት አየር ጤና አካባቢ በሚገኝ ግለሰብ ስልክ ሲደውሉ እንደነበርና የስልኩ ባለቤትም ተጠርጥሮ መያዙን ተናግረዋል፡፡ በባንክ በኩል የአጋቾቹን አድራሻ ለመለየት 5,000 ብር በሠራተኛዋ አካውንት በኩል እንዲገባ መደረጉንና ቃሊቲ ካለ ተመሳሳይ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ብሩ ወጪ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ከሰኞ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ጭምር አጋቾቹን ለማግኘት መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ከፖሊስ ጋር ተባብረው ሲሠሩ መቆየታቸውን የጠቀሱት አቶ አብዱልሀዲ በመጨረሻ ሐሙስ የካቲት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ዘነበ ወርቅ አካባቢ በጥቆማ እንደተደረሰባቸውና አጋቾቹ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ልጆቹ ለወላጆቻቸው እንደተሰጡ የፍለጋ ሒደቱን ተናግረዋል፡፡

ረዳት ኢንስፔክተር ጉታ ቶሎሳ ይህንኑ የልጆቹን እገታ አስታከው እንደተናገሩት ወላጆችም ሆኑ ሠራተኛና ሞግዚት ለልጆቻቸው የሚቀጥሩ ግለሰቦች ተመሳሳይ ወንጀሎች እየተፈጸሙ በመሆኑ ስለሠራተኞቹ በቂ መረጃ አጣርተውና ሕጋዊ ዋስ አስጠርተው ቅጥር እንዲያካሂዱ ነው አሳስበዋል፡፡

ይህን ተጭነው በቴሌግራም ገጻችን ይቀላቀሉን

Post a Comment

አዲስ የድሮ