በደቡብ ክልል በሀያ ቀን ውስጥ 34 ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ መከናወኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አንደኛ ሽናሌ ለኢዜአ እንደገለጹት የዘንድሮ የበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ከጥር 14 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ነው ።
በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች እየተካሄደ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ 34 ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል ።
በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራው ከተከናወኑ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች መካከል የአፈርና የድንጋይ እርከን፣ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮና፣ የተቦረቦሩ ቦታዎችን የማዳፈንና የተጎዱ ስፍራዎችን ከሰውና እንስሳት ንክኪ ማካለል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።
በልማት ስራው አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ፣ በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች የታቀፉ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ናቸው።
እንደ ኃላፊው ገለፃ ለአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ የሚያገለግሉ የተለያዩ አነስተኛ የእጅ መሣሪያዎች ተሰራጭተው ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክለል የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ እቶ ኡስማን ስሩር በበኩላቸው በክልሉ የዘንድሮ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራው ለ35 ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ስራው ባለፉት ዓመታት የተገኙ ልምዶችን በመቀመርና አዳዲስ አስተሳስቦችን ተግባራዊ በማድረግ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ 3 ሺህ 103 ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል ።
በኮንሶ ዞን ካራት ከተማ ዙሪያ የሶርቦ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገረመው ገሌ በሰጡት አስተያየት የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ስራን በዘመቻ ብቻ ሳይሆን እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው አርሶ አደሮች በሳምንት ሁለት ቀናት በቋሚነት እንደሚያከናውኑ ተናግረዋል።
የእርከን ሥራ የኮንሶ ባህል መገለጫ መሆኑን የተናገሩት አርሶ አደሩ የአካባቢው ልምላሜ እንዲጨምር በማድረግ ለግብርና እና ለእንስሳት ልማት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስታውቀዋል።
የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከተጀመረ ወዲህ የአካባቢው ህብረተሰብ የሀሳብና ተግባር አንድነት ከመፈጠር ባለፈ የተጎዱ መሬቶች መልሶ ማገገማቸውን፣የሰብል ምርታማነታቸው መጨመሩንና ሌሎችም በርካታ ውጤቶች በተጨባጭ እየታዩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የልማት ስራውን በማጠናከር በተለይ የተፈጥሮ ጥብቅ ደኖችን በባህላዊ መንገድ ተንከባክበው ለትውልድ ለማስተላለፍ በትጋት እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
አርሶ አደር ከለሰ ገርሾ በበኩላቸው በየጊዜው የሚያካሄዱት የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎች በማሳ ውስጥ የአፈር እርጥበትና ለምነትን ጠብቆ በማቆየት ለማሽላ፣ ጤፍ፣ በቆሎና አደንጓሬ ልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
እንዲሁም ለከብቶች የግጦሽ ሳር በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ማድረጉን ጠቁመው፣ የተፋሰስ ልማቱን ዘንድሮም አጠናክረው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ ባለፈው አመት 3 ሺህ 583 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑታውቋል ።
አስተያየት ይለጥፉ